ኅዳር ሃያ አንድ በዚች ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የበዓልዋ መታሰቢያ ነው።

 

"ጽዮን" ማለት "ጸወን - አምባ - መጠጊያ" ማለት ነው። አንድም በምሥጢሩ "ማሕደረ አምላክ" ማለት ነው። ጽዮን የሚለው ስም በቁሙ ለቅዱስ ዳዊት ተራራና ለኪዳኑ ጽላት ሲያገለግል በትንቢታዊ ምሥጢሩ ግን ለድንግል ማርያም ለቤተ ክርስቲያንና ለዘለዓለማዊት ርስት ያገለግላል።

እግዚአብሔር ከዘመነ አበው በሁዋላ በጊዜው ለእሥራኤላውያን ክብር፣ ሞገስ፣ አምባ የምትሆናቸውን ታቦተ ጽዮንን በቅዱስ ሙሴ አማካኝነት ሰጥቷቸዋል። (ዘጸ. 31፥18) ከዚያም ለ500 ዓመታት ከእነሱ ጋር በመሆኗ በፈጣሪና በእነሱ መካከል ድልድይ ሆና ኖራለች።

ከዚያም ባለቤቱ ሲፈቅድ በዘመነ ሳባ በቀዳማዊ ምኒልክ (እብነ መለክ-እብነ ሐኪም) አማካኝነት ወደ ኢትዮዽያ መጥታለች። እነሆ በሃገራችን የ3ሺ ዓመት ቆይታዋን ልትደፍን የቀራት ጥቂት ዓመታት ብቻ ናቸው። ጌታ እንደ ፈቀደ ቅዱስ መስቀሉንና ታቦተ ጽዮንን ይዘን ይሔው በቸርነቱ እንኖራለን።

ያም ሆኖ ታቦተ ጽዮንን መስረቅ የሚፈልጉ ብዙ ቀሳጢዎች እንዳሉ እናውቃለን። ግን አንጨነቅም። ምክንያቱም የመጣችውም የምትጠበቀውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነውና እንጸልያለን እንጂ አንጨነቅም። በተለያየ ወሬም ራሳችንን አናማጥንም። ባለቤቱ እንድትሔድ ከፈቀደ ደግሞ ማንም ጉልበተኛ አያስቀራትም።

ታቦተ ጽዮን ብዙ ጊዜ "ጽላተ ኪዳን፣ ታቦተ ሕጉ" እየተባለች ትጠራለች። "ጽሌ" ማለት "ሰሌዳ" እንደ ማለት ሲሆን "ጽላት" ደግሞ በብዙ ቁጥር ነው። "ኪዳን" ደግሞ በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል ያለ "ውል - ስምምነት" ነው።

"ታቦት" ማለት "ማሕደር-ማደሪያ" እንደ ማለት ነው። ሕጉ የተጻፈባቸውን ሰላድው "ጽላት" ስንላቸው የጽላቱ ማደሪያ ደግሞ "ታቦት" ይባላል። ጽላት (ታቦትን) ያመጣ ፈጣሪ ነው። በሐዲስ ኪዳንም ምሥጢርና ሐተታ ቢኖረውም 2 ቦታ ላይ ስለ ታቦት ተጠቅሶ እናገኛለን። (2ቆሮ.6፥16 ፣ ራዕይ.11፥19)

በመጨረሻም ኅዳር ሃያ አንድ ቀን ጽዮን ማርያምን የምናከብርባቸውን ምክንያቶች እንመለከታለን።

በዚህች_ቀን

  •  ታቦተ ጽዮን (ጽላተ ኪዳን) ለሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ መሰጠቷን እናስባለን።
  • ታቦተ ጽዮን በምርኮ በሄደችበት በሀገረ ፍልስጤም ዳጎን የተባለ የአህዛብን ጣኦት አድቅቃ በድል የተመለሰችበትን ዕለት በማሰብ።
  • በዘመነ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በአሚናዳብ ሠረገላ ሁና ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ቅዱሱ ንጉሥ በታላቅ ሐሴት በፊቷ ዘመረ። አገለገለ። ምድራዊ ክብሩን እስኪረሳ ድረስ ለታቦተ አምላክ የተቀኘላት በማሰብ።
  • ታቦተ ጽዮን ንጉሥ ሰሎሞን ወደ ሠራላት ቤተመቅደስ በክብር የገባችበትን ዕለት በማሰብ፤
  • የቀደሙ ነብያት ስለእመቤታችን በተለያየ አምሳል ያዩበት ለምሳሌ፦ ነብዩ ዕዝራ በሃገር መንፈሳዊት፣ ሕዝቅኤል በተዘጋች ቤተመቅደስ፣ ዘካርያስ በተቅዋመ ወርቅ ወዘተ ያዩበትን ዕለት በማሰብ፤
  • ቀዳማዊ ምኒሊክ ከዐሥራ ሁለቱ ነገድ እስራኤል የበኩር ልጅ ጋር ሊቀ ካህናቱን  አዛሪያስንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የደረሰበትን ዕለት በማሰብ፤
  • በዘመነ አፄ ባዜን (በ4 ዓ/ም አካባቢ) አማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ወደ አክሱም ጽዮን በስደት መጥታ ገብታለች። በዚህ ጊዜም 2ቱ ጽዮኖች ሲገናኙ ታላቅ ብርሃን አክሱምን ውጧታልና ይህንንም በማሰብ፤
  • በአብርሃ ወአፅብሃ ዘመነ መንግስት ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ አዋጅ የታወጀበትን በማሠብ፤
  • አብርሃ ወአጽብሃ በወርቅና በዕንቁ ያሠሩት ባለ አሥራ ሁለት ክፍል ቤተ መቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ዕለት በመሆኑ፤
  • በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዮዲት ጉዲት አብያተ ክርስቲያንን ስታቃጥል ታቦተ ጽዮንን ይዘው ወደ ዝዋይ ሀይቅ ከተሰደዱ በኋላ ዘመነ ሰላም ሲጀመር አክሱም በነበሩ ካህናት አስታዋሽነት ከዝዋይ ወደ አክሱም የገባችበት ዕለት በመሆኑ፤

በእነዚህ ምክንያቶች በመላው ኢትዮጵያ በተለይም በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ከፍ ባለ መንፈሳዊ በዓል እናከብራለን።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በጸሎቷ የሚገኝ በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ይኑር።

እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ!

ምንጭ  :  (ስንክሳር ዘተዋሕዶ ፌስቡክ ገጽ)

ተጨማሪ ንባብ ፡ ታቦተ ጾዮን -  ከማህበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ