ምስጢረ ጥምቀት / ክርስትና

ምስጢረ ጥምቀት ከሥጋ የተወለደ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልዶ የእግዚአብሔርን የጸጋ ልጅነት የሚያገኝበት ታላቅ ምስጢር ነው፡፡

ይህም ምስጢር ከሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ቀዳሚው ስለሆነ “የክርስትና በር / መግቢያ” ይባላል፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢረ ጥምቀትን ራሱ ተጠምቆ አርአያ በመሆን፣ ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ መሆኑን በማስተማር፣ እንዲሁም ሐዋርያቱ እንዲያጠምቁ በማዘዝ መስርቶልናል፡፡

በዚህም መሠረት በሥላሴ ስም የተጠመቀ ሰውም አምላኩ ክርስቶስ፣ እምነቱ ክርስትና፣ ማንነቱ ክርስቲያን፣ እናቱ ቤተክርስቲያን ይሆናሉ፡፡ ክርስትና ለምን ተባለ ቢሉ የሰው ልጆች ጥምቀቱን ከተጠመቁ በኋላ በክርስቶስ ክርስቲያን፣ በወልድ ደግሞ ውሉደ እግዚአብሄር /የእግዚአብሄር ልጆች/ ተብለው ይጠራሉና ነው።

ስለዚህም ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምስጢረ ጥምቀትን የእምነት መሠረት በመሆኑ ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት፣ ተፈጻሚ ምስጢር በመሆኑ ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን በመመደብ ታላቅ ቦታ ትሰጣለች፡፡

የሰው ልጅ ሁሉ አምኖና ተጠምቆ በቀናችው የሃይማኖት መንገድ ተጉዞ ዘላለማዊ ሕይወትን ይወርስም ዘንድ የሕይወትን ቃል ትመግባለች፡፡

በጥምቀት ከማይጠፋ ዘር የወለደን፣ በሞቱና በትንሣኤው እንመስለው ዘንድ ተጠምቆ ተጠመቁ ያለን የቅዱሳን አምላክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀትም የልጅነት ጸጋ ሰጠን እንላለን።

 

የሕፃናት ጥምቀት

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕጻናትን በ40 እና በ80 ቀን ስታጠምቅ ምስጢራትን፣ ምሳሌዎችን፣ ትውፊትን እንዲሁም የጌታንና የሐዋርያትን አስተምህሮ መሠረት አድርጋ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንደሚናገረው ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ኃጢአት በደል አለባቸው ብላ ሳይሆን ከለጋነት ዕድሜያቸው ጀምረው ፍቅሩን እያጣጣሙ እንዲያድጉ የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ጸጋ ልትሰጣቸው ነው፡፡

ቤተክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ያውቃሉ ወይም አያውቁም ብላ አይደለም፡፡ የቤተሰቦቻቸውን እምነትና ፈቃድ ምስክር በማድረግ ነው እንጂ፡፡

  1. አዳምና ሔዋን በተፈጠሩ በ40 እና በ80 ቀናቸው ወደ ገነት መግባታቸው (ኩፋ 4፡9)፡፡
  2. እስራኤል መስዋዕት ይዘው በ40 እና በ80 ቀን ወደ ቤተመቅደስ እንዲመጡ መታዘዛቸው (ዘሌ 12፡1-8)፡፡
  3. በኦሪቱ ሕፃናትም አዋቂዎችም ተገርዘው የተስፋው ወራሾች ነበሩና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፍ 17፡1-5 ቆላ 2፡11-12)፡፡
  4. በባህረ ኤርትራ የተሸገሩት ሕፃናትም ጭምር ነበሩና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (1ኛ ቆሮ 10፡1-2)፡፡
  5. ወደ ኖኅ መርከብ የገቡት መላው ቤተሰብ ነውና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፍ 7፡1-17 1ኛ ጴጥ 3፡20-22)፡፡
  6. ሕፃናት በማኅፀን ሳሉ መንፈስ ቅዱስ ከሞላባቸው ሲወለዱ እንዳይጠመቁ የሚከለክለቸው ምንድን ነው (ሉቃ 1፡15 ኤር 1፡4-5)፡፡
  7. ሐዋርያትም ካስተማሩ በኋላ ቤተሰቡን ሙሉ ያጠምቁ ነበር (ሐዋ 10፡44-48 11፡13-14 16፡15 16፡43)፡፡
  8. ጌታችንም “ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ…” ያለው ሕፃናትንም ይመለከታል (ዮሐ 3፡8)፡፡
  9. ጌታችንም “ሕጻናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው” ብሏል (ማቴ 19፡14)፡፡
ጥምቀት አንዲት ናት!

የልጅነት ጥምቀት አንዲት ናት፤ አትደገምም (ኤፌ 4፡5) “ኃጢአት በሚሠረይባት አንዲት ጥምቀት እናምናለን” እንዲል፡፡

ከወላጆቻችን በሥጋ የምንወለደው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ሁሉ ከውሃና ከመንፈስም ከእግዚአብሔር የምንወለደውም (የምንጠመቀው) አንድ ጊዜ ብቻ ነው ።

የጥምቀት ምሳሌ የነበረው ግዝረት አንድ ጊዜ ብቻ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም አንድ ጊዜ ነው (ቆላ 2 ፥ 11)። ከጌታ ሥጋና ደም የምንሳተፍበት ምሥጢር በመሆኑ ጌታም የሞተውና የተነሳው አንድ ጊዜ ነውና አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን (ሮሜ 6፡3)።

አንድ ሰው በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ በሌላ ሃይማኖት ገብቶ እንደገና ቢጠመቅ ወይም ከሌላ እምነት ተከታይ ጋር ጋብቻ ቢመሠርት በንስሓ ከተመለሰ በኋላ መጽሐፈ ቄደር ተጸልዮለት ይጠመቃል።

ይህ ግን ሁለተኛ ጥምቀት ሳይሆን የንስሓ ጥምቀት ይባላል። ከኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት (Oriental Churches) በቀር በሌላ ማንኛውም ቤተክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ አምኖ የሚመጣ ሰው ቢኖር እንደገና ይጠመቃል።

 

ስርዓተ ተክሊል

ተክሊል ማለት ክብር ማለት ሲሆን ቃሉም ከለለ አከበረ ጋረደ ከሚለው ግስ የወጣ ዘር ነው።

በተክሊል ወንድ «የባሏ ክብር ናት» የተባለች ረዳቱን በፅኑ ኪዳን ወይም በመንፈስ ውል የሚቀበልበት ስለሆነ የተክሊል ጋብቻ የከበረ ነው፣ ለሴቷም እንዲሁ። እንዲሁም በእግዚአብሄር ስለሚቀደስና ስለሚከበር የተክሊል ጋብቻ ቅዱስ ነው። ዕብ1÷12

የመጀመሪያው ጋብቻ በእግዚአብሄር ፈቃድ በኤደን ገነት እንደተመሰረተ ሁሉ ዛሬም ስርአተ ተክሊል በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይፈፀማል። ዘፍ1÷22

በመሆኑም ስርአተ ተክሊሉ የተሟላ የሚሆነው ስርዓተ ተክሊሉ ተፈፅሞ ወጣቶች ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ብቻ ነው።

 

ለዚህ ክብርና የተቀደሰ ጋብቻ ለመብቃትም መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ። እነዚህም

1/ የሃይማኖት አንድነት ያስፈልጋል። 

2/  ድንግልናን መጠበቅ / ከጋብቻ በፊት ከሚደረግ ማንኛውም የግብረ ሥጋ ግንኙነት መታቀብ

3/ በሁለቱ ጥንዶች መካከል እውነተኛ መፈቃቀድ ሊኖር ይገባል፡፡

4/ የአእምሮም ሆነ የአካላዊ ብቃት ሊኖረን ይገባል።

6/  የንስሐ አባት ምስክርነት ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ጋብቻ አንድ ለአንድ የሚፈጸም ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ኤፌ 5፡32

"ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት፡፡" 1ቆሮ7፡2

ይህንን ሰማያዊ ትእዛዝ ስንመለከተው ባሎች ወይም ሚስቶች የሚል ሐሳብ አለመኖሩ አንድ ለአንድ የሆነውን ጋብቻ ብቻ መፈጸም እንዳለብን ያስገነዝበናል፡፡ ከአንድ በላይ ማግባት አለመፈቀዱን ለመረዳት ሌላው የመጀመሪያዎቹ አዳምና ሔዋን ያደረጉትን ልዩ ጋብቻ ማየቱ በቂ ነውና፡፡ዘፍ 2፡23

ቤተክርስቲያን ሁለት ዓይነት የጋብቻ ሥርዓትን በሐይማኖት ለጸኑት፤ ቀኖናቸውን ለፈጸሙት እና ስርዓቱን አክብረው ተዘጋጅተው በፍቃዳቸው ጋብቻን ለመፈጸም ለቀረቡት ሁሉ ትፈጽማለች፡፡

 

ሁለቱ ዓይነት የጋብቻ ሥርዓቶች የምንላቸው ፡-

1ኛ. በተክሊል የሚፈጸም እና

2ኛ. ያለ ተክሊል የሚፈጸም ሥርዓቶች ናቸው፡፡

1ኛ. በተክሊል የሚፈጸም ፡- ይህ በድንግልና ላሉ ጥንዶች የሚፈጸም ሥርዓት ሲሆን ስለ ድንግልናቸው ክብር የሽልማት ምልክት የሆነውን የድል አክሊል ይጭናሉ፡፡ የክብርን ካባ ይለብሳሉ፤ በዚህም ሌሎች ድንግልናቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸውና ለዚህ ክብር እንዲበቁ ለማስተማሪያ ትጠቀምባቸዋለች፡፡ ይህ ምሥጢር የሚፈጸመው በተክሊል ነው፡፡

2ኛ. ያለ ተክሊል የሚፈጸም ፡- ይህ ደግሞ ድንግልናቸውን በፍላጎታቸው በማወቅም ባለማወቅም ያጡ ጥንዶች የሚፈጽሙት ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ ጥንዶች የሚያደርጉት ጋብቻ እንደ ቤትክርስቲያን ስያሜ የመዓስባን ጋብቻ ይባላል፡፡

 
ምስጢረ ቁርባን

ቁርባን ቃሉ የሱርስትና/የግሪክ ሲሆን ትርጉሙ በቁሙ መንፈሳዊ አምኃ (ስጦታ)፣ መስዋዕት፣ መባዕ፣ ለአምላክ የሚቀርብ የሚሰጥ ገንዘብ ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የጌታ እራት››፣ ‹‹ምስጢራዊው እራት››፣ ‹‹አንድ የመሆን ምስጢር›› ይሉታል፡፡ ቁርባን የሚለውን ቃል አባቶች ሲያመሰጥሩት ሰው ለአምላኩ (ለፈጣሪው) የሚያቀርበውን አምኃ በሙሉ የሚያካትት ሲሆን፣ ነገር ግን በዚህ ጽሁፍ ላይ የምንመለከተው ግን ስለ አማናዊው ስጦታ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ነው፡፡

ከሰው ለእግዚአብሔር የቀረበ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ለሰው ሁሉ የተሰጠ የዘላለም ሕይወትን ስለምንካፈልበት አምላካዊ ጥበብ ነው፡፡ ሰው ለመስዋዕት የሚሆነውን ቀላል ነገር ያቀርባል፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የሰውን መታዘዝና እምነት አይቶ የሚያልፈውን ወደማያልፈው፣ ምድራዊውን ወደ ሰማያዊው፣ ጊዜያዊውን ወደዘላለማዊው ይለውጣል፣ ይህም ምስጢረ ቁርባን በመባል ይታወቃል፡፡

ምስጢረ ቁርባንን የመሠረተው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራውን አንስቶ ባረከ፤ ቆርሶም ለደቀመዛሙርቱ ሰጠና እንካችሁ ብሎ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖ ሰጣቸው፡፡ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ፤ ስለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው፡፡›› (ማቴ 26፡26) በማለት የምስጢረ ቁርባንን አመሠራረት ጽፎታል፡፡ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳን ሲቀርቡ የነበሩ መስዋዕቶችን ሁሉ ምሳሌው አድርጎ በማሳለፍ የራሱን መስዋዕትነት ካቀረበ በኋላ ቀድሞ የነበሩትን ነፍሳት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድርስ የሚመጡትን ሁሉ አንድ ጊዜ ባቀረበው መስዋዕት የሚያድን ስለሆነ ምስጢሩ ይፈጸም ዘንድ ከሞቱ አስቀድሞ አስተማረ፡፡ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ የወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው›› በማለት እስከዓለም ፍጻሜ የሰው ልጅ ሌላ መስዋዕት ሳያስፈልገው በአምላካችን ሥጋና ደም ሕይወት እንደሚያገኝ አስተማረ፡፡ የምስጢረ ቁርባንን ትምህርት በወቅቱ የነበሩ አይሁድ ሰምተው ምስጢሩ አልገባቸው ሲል ‹‹ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይቻላል›› በማለት ጠይቀው ነበር፡፡ ደቀመዛሙርቱም ትምህርቱ ከብዷቸው ነበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ ግን ምስጢሩን ተረድተው ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ (ሐዋ 2፡43፣ 1ኛ ቆሮ 11፡20)

ቅዱስ ቁርባን ለሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አክሊል ነው፡፡ እንዲያውም ምስጢረ ምስጢራት ይባላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ተጠማቂ ተጠምቆ እንደወጣ ቅዱስ ቁርባን መቀበል አለበት፡፡ አንድ ተነሳሒ ቀኖናውን ሲጨርስ በካህኑ ፈቃድ ንስሐውን በቅዱስ ቁርባን ያትመዋል፡፡ በቅዱስ ጋብቻ ለመኖር የወሰኑ ተጋቢዎች ከሥርዓተ ተክሊል በኋላ አስቀድሰው ቅዱስ ቁርባንን ይቀበላሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ቅዱስ ቁርባን የምስጢራት ምስጢር መባሉ ትክክል ነው፡፡ ቅዱስ ቁርባን የምስጢራተ ቤተክርስቲያን ሁሉ የበላያቸው፣ መክብባቸውና መፈጸሚያቸው የሆነበት ምክንያት ጌታ የሰውን ልጅ ለማዳን በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ ሥጋውን በመቁረስ ደሙንም በማፍሰስ ካሳ የከፈለበትን፣ የማዳን ሥራውን የፈጸመበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥና የሚመሰክር ከመሆኑ ጋር ምዕመናን ከሥጋውና ከደሙ ተካፋይ እንዲሆኑ በማብቃት የሕይወትን ጸጋ እንዲቀበሉ ስለሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህም ሌሎቹ ምስጢራት ሁሉ በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት የምስጢራቸውን ትርጉምና ፍጻሜ ያገኛሉ፡፡

 

ጸሎተ ፍትሃት

ፍትሐት ማለት ከኃጢአት እስራት መፍታት ወይም መፈታት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ለሞቱ ሰዎች የሚደረገው ጸሎት ጸሎተ ፍትሐት ይባላል።

የሙታን ነፍሳት ከሥጋ እንደተለዩ እስከ እለተ ምጽአት ድረስ በማረፊያ ቦታ ይቆያሉ እንጂ በቀጥታ ወደ መንግስተ ሰማይ ወይም ወደ ገሃነመ እሳት እንደማይላኩ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውና የምታስተምረው ትምህርት ነው፤ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ የሚቆዩበትም ቦታ ለጻድቃን ገነት ሲሆን ለኃጢአተኞች ደግሞ ሲኦል ነው። የጻድቃን ማረፊያ ቦታቸው ገነት መሆኑን ለማመልከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በነበረ ጊዜ ንስሐ ለገባው ወንበዴ፡ “በእውነት እልሃለው ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎታል። ሉቃስ 23፥43። የኃጢአተኞች መቆያ ደግሞ ሲኦል መሆኑን ለማመልከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሀብታሙ ሰውና በድኻው አልዓዛር ምሳሌ ትምህርቱ ሀብታሙ ሰው በሲኦል ውስጥ እንደነበረ ገልጿል። ሉቃስ 16፥23፡፡ በሙታን ትንሣኤ ጊዜ የምንነሳው በውርደት ወይም ክብር በሌለው ሁናቴ በመሬት ውስጥ እንደተቀበርነው ሳይሆን፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው በክብር፣ በኃይልና በመንፈሳዊነት ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥42። ከዚያም በኋላ ወደ ክርስቶስ የፍርድ ፊት እንቀርባለን። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፥10፤ ራዕይ 6፥9፡፡

ይቅርታ በዚሁ ዓለምና በሚመጣውም ዓለም መኖሩን ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል። ማቴዎስ 12፥32፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ለነበረው ለኦኔሲፎር “በመጨረሻው ቀን ምሕረትን ይስጠው” ብሎ ጸልዮለታል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 1፥18። ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ጸሎት ለሞቱ ሁሉ ትጸልያለች።

ለሞቱ ሰዎች መጸለይ ደግሞ በጥንት በዘመነ ብሉይም ነበረ። ጀግናው ይሁዳ መቃብዮስ በጦርነት ለሞቱ ወታደሮቹ የኃጢአት መሥዋዕት ይደረግላቸው ዘንድ ሁለት ሺህ የብር ድራህም አሰባስቦ ወደ ኢየሩሳሌም ልኳል። 2ኛ መቃብያን 12፥43፤ ዕዝራ ሱቱኤል 6፥35። አይሁድ ለሙታን ሲጸልዩ ዳዊት ይደግማሉ።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በተላከው የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ላይ ባደረገው ስብከቱ እንዲህ ብሏል “አንድ ሰው ኃጢአተኛ እንደሆነ ቢሞት የምንችለውን ያኽል ልንረዳው ይገባል። የምንረዳውም በለቅሶና በሐዘን ሳይሆን በጸሎት፣ በምጽዋትና በቁርባን ነው። የዓለምን ኃጢአት ወደ ተሸከመው የእግዚአብሔር በግ ስለ ሙታን የምንጸልየው እነርሱ መጽናናትንና እረፍትን እንዲያገኙ ብለን ነው እንጂ በከንቱ አይደለም። ጻድቁ ኢዮብ ስለልጆቹ ያቀርብ የነበረው ቁርባን ጠቀሜታ ከነበረው ስለ ሙታን የምናቀርበው ቁርባን ምንኛ የበለጠ ጠቀሜታ ይኖረው?

ጸሎተ ፍትሐት የሚደረገው ሳይታወቁ ለተፈጸሙ ኃጢአቶች፣ በድብቅ ለተፈጸሙ ኃጢአቶች፣ እንዲሁም ለተረሱ ኃጢአቶችና ኃጢአት ሰሪው ኃጢአት መስራቱ ሳይሰማው የሚሰራቸው ኃጢአቶች ናቸው። እንደነዚህ ያሉት ኃጢአቶች ከሰው ተፈጥሮ ደካማነት የተነሳ የሚፈጸሙ መሆናቸው ቢታመንበትም በእግዚአብሔር ፍትሕ በኩል ግን እንዲህ አይደለም። እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረው “አንድ ሰው ባለማወቅ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ አንዱን ቢተላለፍ በደለኛ ነው” ብሎ ነው፡፡ ዘሌዋ 5፥17።

ሰው አፈር የሆነውን ሥጋ የለበሰ እንደመሆኑ መቼም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ከኃጢአት የነፃ ሊሆን አይችልም። “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናታልላለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” እንዲሉ። 1ኛ ዮሐንስ 1፥60። እግዚአብሔር በንስሐ የሚመለሰውን ሰው በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ይቀበለዋል።፡ ለምሳሌ በሞት አፋፍ ላይ የነበረውና ከጌታችን ጋር ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ ንስሐው ተቀባይነት ያገኘው በመጨረሻው ደቂቃ ነው። ስለዚህ ንስሐ የገባ ሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ማን እንደሆነ ስለማናውቅ ለሁሉም እንጸልያለን። ለሙታን የሚደረግ ጸሎት ወይም ጸሎተ ፍትሐት ዘወትር ጠቃሚ ነው። ወደ ገነት ለመግባት ላልታደሉት ጸሎቱ ዕድላቸውን ከመቃብር በላይ ያደርግላቸዋል። በሰማይ ስማ ሰምተህም ይቅር በል። 2ኛ ዜና 6፥21። በገነት ላሉትም እንደ ታላቅ ብርሃን እየፈነጠቀ ታላቅ ደስታን ይሰጣቸዋል። በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያን በፍትሐት ጸሎት አምና ለልጆቿ ምህረትን ትለምናለች፣ ይህንኑም ታስተምራለች።

 

ስርዓተ ቅዳሴ

ቅዳሴ የሚለው ቀደሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን አመሰገነ፣ ምስጋና አቀረበ ማለት ነው። ቅዳሴ ደግሞ ምስጋና ማለት ነው። በቤተ ክርስቲያን በርካታ የምስጋና ዓይነቶች ያሉ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ማኅሌት፣ ሰዓታት፣ ኪዳን (ስብሐተ ነግሕ) እና ቅዳሴ ናቸው። ማንኛውም አገልግሎት ከተሰጠ በኋላ በመጨረሻ የሚቀርበው የጸሎት፣ የምስጋና ክፍል ቅዳሴ ነው። የማኅሌቱ፣ የሰዓታቱ፣ የስብሐተ ነግሑ አገልግሎት ከተሰጠ በኋላ መቋጫው፣ መደምደሚያው ቅዳሴ ነው። ምክንያቱም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደሙ የሚፈተትበት፣ በካህናት የሚቀርበው መስዋዕተ እግዚአብሔር የሚያርግበት፣ ኅብስትና ወይኑ ወደ ፍጹም አማናዊ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔርና ደመ ወልደ እግዚአብሔር የሚቀየርበት የምስጋና ክፍል ስለሆነ ነው። ማኅሌት ቢቆም ሰዓታት ቢደርስ ያለ ቅዳሴ ሊሆን አይችልም። ማኅሌትና ሰዓታት በሌለበት ግን ቅዳሴ ተቀድሶ ሥጋ ወደሙ ይፈተታል። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ለቅዳሴ ሚሰጠው ትኩረት ልዩ የሆነው ለዚህ ነው።

አንድ የቅዳሴ ጸሎት ሶስት ክፍሎችን የያዘ ሲሆን እነዚህም፦

1ኛ.  የመዘጋጃ ቅዳሴ 2ኛ.  የንባብ ቅዳሴ 3ኛ. ፍሬ ቅዳሴ ናቸው።

ቅዳሴ አብዛኛውን ጊዜ  5 ሆነው ይቀደሳል፣ ይኸው የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሣሌ ነው፡፡

ነገር ግን ከዚያም በሚያንስም ሆነ በሚበዛ ሰው ቅዳሴን መቀደስ ይቻላል።

ለምሳሌ

7  ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ይመስላሉ።

13  በ12ቱ ሐዋርያት እና በጌታችን ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ፤

24  በሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ። ይህ የሚሆነው እንደ ካህናቱ ብዛት ነው።

ጭራሽ ካህን ከጠፋ ደግሞ 1 ቄስና 1 ዲያቆን ሆነው መቀደስ ይችላሉ።  ሁለትነታቸው የመለኮትና የትስብዕት (የሥጋ) ምሳሌ ሆነው ይቀድሳሉ። በሦስት ከሆነ በሦስቱ ሥላሴዎች አራት ከሆኑ በ4ቱ ወንጌላውያን ይመሰላሉ።

ከሁለት ባነሰ ግን 1 ሆኖ ግን ቅዳሴ አይቀደስም፤  የቤተክርስቲያን ሥርዓት/ቀኖና ይከለክላል፡፡